የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ተከሳሾች ላይ ከ195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡
ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነሳው በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ፣ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ (ዶ/ር) ፣ የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አብርሐም ባያብል (ኢ/ር)፣ የግዢ ዳይሬክተር ሊበይ ገልገሎ፣ የግዢ ዳይሬክተር ቦሩ ህርቦዬ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህርና የቢኤች ዩ አማካሪ ለታ ድሪባን ጨምሮ ጠቅላላ ስራ ተቋራጮችና የቢዳሩ ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጆች ይገኙበታል።
በተከሳሾቹ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አራት ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክሶችን መስርቷል።
በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግስት ግዢ አዋጅን በመተላለፍ በ2012 ዓ.ም በያዙት ቃለ ጉባኤ መሰረት ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ ቢኤች ዩ ለተባለ አማካሪ ግዢው በቀጥታ እንዲፈጸም በማኔጅመንት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ውል ሲዋዋል ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት 1ኛ ተከሳሽ ውል ሰጪ ሆነው 7ኛ ተከሳሽ ውሉን በመፈረም በ5ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ መሰረት በአንደኛ ተከሳሽ ስም ለተመዘገበው አማካሪ ድርጅት ያለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲውን የመተዳዳሪያ እና የግዢ አዋጅ በመተላለፍ የ14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ግዢ በመፈጸምና 116 ሚሊየን 389 ሺህ 964 ብር ማሽነሪዎችን በስጦታ ያገኙ በማስመሰል ያለአግባብ 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ተከሳሾች በተሽከርካሪ ግዢ ጥቅም ማግኘታቸው ተመላክቷል።
ተከሳሾቹ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በቀጥታ ግዢ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ ከሌሎች ተከሳሾችና ከስራ ተቋራጮች ያለአግባብ ካለ ግልፅ ጨረታ ግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በዋና እና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው የክስ ዝርዝርም በችሎት ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾቹ ከጠበቃቸው ጋር ተማክረው የፊታችን ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ፍድር ቤት ቀርበው ክሱን በንባብ ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ