የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው- የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ ገለጹ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን መቋጫ ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስለመዘጋጀቱም አረጋግጠዋል።
በአገራዊ የምክክር ሂደቱ እንደ አገር እየፈተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት መነጋገርና የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንዲሁም ምክክሩ እንዲሳካ የሁሉም ሃላፊነት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም ሕገ ወጥ ድርጊቶች መከላከልና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጋራ ጥረታችን ሊታከልበት ይገባልም ነው ያሉት።
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ ቁርጠኛ በመሆን ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ኮሚሽነሮችም ተሹመውለት ስራ መጀመሩ ይታወሳል።