Fana: At a Speed of Life!

ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸውን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀን ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ እነረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው እና ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቀደ።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ14 ቀን ጊዜ ለፖሊስ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በትናንትናው እለት በተጠርጣሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፣ ፕሮፌሰር ማዕረጉ ቢያብን፣ ሰለሞን ልመንህ እና ሄኖክ አዲስ፣ ንዋይ ዮሐንስ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻዎችን እና የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን መከራከሪያ ነጥብ ተመልክቶ መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ለዛሬ በያዘው ቀጠሮ መሰረት ዛሬ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል።

በዚህም የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪዎች ዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራ የማድረግ አስፈላጊነትን በማመን ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ፎቷችን ተለጥፎ ሽብርተኛ ተብለን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታችንን በሚጥስ መልኩ በመገናኛ ብዙሃን ተዘግቦብናል ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ፍርድ ቤቱ መርምሮ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩትን ለማፈላለግ በሚል የቀረበ ዘገባ እንጂ ወንጀለኛ ተብሎ የቀረበ ባለመኖሩ ህግ ተጥሷል ለማለት አያስችልም ሲል አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጎታል።

 

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.