የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የሁለት ሣምንታት የዋስትና ጊዜ ተፈቀደላቸው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓኪስታን ፍርድ ቤት በዚህ ሣምንት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ለእስር ለተዳረጉት የቀድሞው የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን የሁለት ሣምንታት የዋስትና ጊዜ ፈቀደ።
የኢስላማባድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርብ ዕለት በዋለው ችሎት ነው በሙስና ሰበብ በሀገሪቷ የፀረ-ሙስና ኤጀንሲ በድንገት ተይዘው እስር ላይ ለሚገኙት ለቀድሞው የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር የዋስትና መብታቸውን ያረጋገጠው።
ኢምራን ካን በዛሬው ዕለት በኢስላማባድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ያገኙት በድንገት ታፍነው መታሠራቸው ከተሰማ በኋላ ሐሙስ ምሽት ላይ የሀገሪቷ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “እስራቱ ሕጋዊ አይደለም” በሚል በሠጠው መመሪያ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡