Fana: At a Speed of Life!

ሃንጋሪ ከአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን መተላለፍ የነበረበትን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ማገዷ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃንጋሪ ከአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን መድረስ የነበረባቸው 544 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎችን ማገዷ ተሰማ።

መሳሪያው ከአውሮፓ ኅብረት በአውሮፓ የሠላም ተቋም በኩል ለኪየቭ የሚላክ እንደነበር አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

ሃንጋሪ መሳሪያው “ዩክሬን ለማስታጠቅ ብቻ የሚውል ከሆነ” በእኔ በኩል አያልፍም ለዚህ ዋስትና ይሰጠኝ ስትል ጠይቃለች።

የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን አሜሪካ መራሹ የምዕራባውያን ጎራ ለዩክሬን በቡዳፔስት በኩል ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ማሳለፍ እንደማይችል ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው የአውሮፓ የሠላም ተቋምም ሆነ ምዕራባውያኑ ለአንድ ወገን ያደላ ሳይሆን “እሳቤያቸው ዓለም አቀፋዊ” ሊሆን ይገባል።

የአውሮፓ የሠላም ተቋም መሰል የመሳሪያ አቅርቦት ለዩክሬን ሲልክ ይህኛው ለሥምንተኛ ዙር ነበር ተብሏል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮላድሜር ዜለንስኪ ሩሲያ ለምታደርስባቸው ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ለመሥጠት ምዕራባውያኑ የከባድ መሳሪያ አቅርቦቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

ዜሌንስኪ ለዚሁ ጥያቄዎቻቸው ጣሊያንን ፣ ጀርመንን፣ ብሪታንያን እና ፈረንሳይን ዞረው አዳርሰዋል፡፡

የሃንጋሪው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ሺጃሪቶ ÷ ምንም እንኳን ሃንጋሪ የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን የሚያደርገውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ባትደግፍም አቅርቦቱን ግን የማገድ ፍላጎት እንደሌላት ሲገልጹ መቆየታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.