አቶ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚክሃሊ ቦግዳኖቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስምምነት ባደረጉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
እንዲሁም አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአማርኛ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ በሁለቱ አገራት ወዳጅነት ላይ ያተኮረ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸው የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ከ125 አመታት በፊት የጀመረና እየተጠናከረ የመጣ መሆኑን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን ግንኙነት እንዲያጠናክርና ኢትዮጵያ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የምታደርገውን ሽግግር እንዲደግፉ እንዲሁም የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ተቀብለው አንዲያስተምሩ ጠይቀዋል ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅት አድርገው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አቶ አገኘሁ÷ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የኢነርጂ ምክትል ሚኒስትር ፣ከሩሲያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ እንዲሁም ከሩሲያ ዩናይትድ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸውም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡