በኢትዮጵያ በሰላም ማጽናት፣ በትምህርት፣ በባህልና በስፖርት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል-ሚኒስትሮች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰላም ማጽናት፣ በትምህርት፣ በባህልና በስፖርት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን ሚኒስትሮች ገለጹ።
የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እና የሦስተኛው ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም÷ያለ ሠላም እድገትና ብልጽግና ማምጣት አይቻልም ያሉ ሲሆን ይህንን በመገንዘብ ሀገሪቱ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ለመቀየር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነት ለማቆም የተደረገው የሰላም ስምምነት አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸው የሰላም ሥምምነት አተገባበሩም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላም ለማረጋገጥ፤ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ በማድረግ አበረታች ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)በበኩላቸው÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት እስከ ስምንተኛ ክፍል ለማስፈጸም የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በተደረገው ግምገማም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው መነሳቱን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ እንደተናገሩት÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስፖርትና በባህል ልማት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው በግምገማው ቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
በዚህም በስፖርት ዘርፍ ዋና ዋና የሚባሉ የስታዲየም ግንባታ ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅና በተለያዩ አካባቢዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታዎችን ማስፋፋት ላይ ይሰራል ነው ያሉት።
ከባህል ልማት አኳያ በተለይም የባህል ትስስርን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት መስራት እንዳለበት መነሳቱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።