የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የፈጠረልንን ዕድል በመጠቀም ህዝባችንን ልንክስ ይገባል – አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ረዳ ከተለያዩ የክልሉ ከተሞችና የገጠር ወረዳዎች ከተውጣጡ የንግድ ማሕበረሰብ ተወካዮችና ባለሀብቶች ጋር ዛሬ ተወያዩ።
መድረኩ፥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የያዛቸው እቅዶች፣ አቅጣጫዎችና ወቅታዊ ጉዳዮች በመወያየት የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም በክልሉ በነበረው ጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ተመሳሳይ ግንዛቤ ይዞ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት እንደሆነ ተገልጿል።
መድረኩን የመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ “የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የፈጠረልንን ዕድል በመጠቀም ህዝባችንን ልንክስ ይገባል” ሲሉ ገልፀዋል።
“ይህ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ያጋጠሙን ከባድ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በፍጥነት ለመውጣት የሚያግዝ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን በተሰማራንበት ዘርፍ ልንረባረብ ይገባል” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከጊዜያዊ መስተዳደሩ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።