የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጤናማ ለማድረግ የአመራሩ ቅንጅታዊ አሠራር ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኑሮ ውድነትን፣ ሕገ-ወጥ ንግድንና የፀጥታ ችግርን በመከላከል የኢኮኖሚ ዕድገቱን ጤናማ ለማድረግ የአመራሩ ቅንጅታዊ አሠራርና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ።
የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የመንግሥት የየዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የምክር ቤት አባላትና የተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል።
በግምገማው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ እንደገለጹት÷ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድ ሥርዓቱን እየፈተኑ ነው።
የንግድ ሰንሰለቱ መራዘሙን ተከትሎ መሠረታዊ ሸቀጥ አትክልትና ፍራፍሬ ዝውውር ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍም ከክልሎች ጋር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው÷ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ በመሆኑ ለመከላከል ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በርካታ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑ እና አመራሩና ሕጋዊ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ እየተሳተፉ መሆናቸውና ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው አንስተዋል።
አደጋውን ለመቆጣጠር የሎጂስቲክስና የቴክኖሎጂ አቅሞች ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቅርቡ የወጪና ገቢ ንግድ ምርቶችን በከፍተኛ ብቃት መፈተሽ የሚያስችል ሥርዓት እንደሚጀመር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡