Fana: At a Speed of Life!

በተወሰኑ የአሜሪካ ግዛቶች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት ሊሆኑ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተወሰኑ የአሜሪካ ግዛቶች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአገልግሎት ክፍት ሊሆኑ ነው።

ጆርጂያ፣ ኦክላሆማ እና አላስካ ግዛቶች የተወሰኑ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ፈቃድ ሰጥተዋል።

ይህን ተከትሎም በጆርጂያ እና ኦክላሆማ የተለያዩ የውበት ሳሎኖች ወደ ስራ እንዲገቡ ይሁንታ አግኝተዋል።

በአንጻሩ በአላስካ ደግሞ ምግብ ቤቶች ለተጠቃሚዎች አገልግሎት እንዲሰጡ የተጣለው እገዳ ተነስቶላቸዋል ነው የተባለው።

ተጠቃሚዎችም አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የወጡ መመሪያዎችን መተግበር ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

የአሁኑ እርምጃ ግን በሃገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በቀጣይ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ነው በሚል ከጤና ባለሙያዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።

የግዛቶቹ እርምጃ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ መልዕክት አስተላልፈዋል ከተባለ በኋላ የወጣ መሆኑም ተነግሯል።

ፕሬዚዳንቱ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ለሽንት ቤትና ወለል ማጽጃ የሚያገለግሉ መርዛማ ማጽጃዎችን ቢጠቀሙ ነጻ ይሆናሉ የሚል ንግግር ማድረጋቸው ተሰምቷል።

ይህን ተከትሎም ከሃገሬው ዜጎች፣ የህክምና ባለሙያዎችና ከአምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣን አስተናግደዋል።

ትራምፕ ግን ንግግራቸው “ለፌዝ የተባለ” እና “ከአውዱ ውጭ የተተረጎመ” ነው የሚል ማስተባበያ ሰጥተዋል።

አሁን ላይ በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 51 ሺህ ሲያልፍ ከ890 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.