በድሬዳዋ ከተማ በጎርፍ አደጋ የአራት ሰዎች ህይዎት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ በትናንትናው ዕለት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የአራት ሰዎች ህይዎት ማለፉን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ዝናቡ ትናንት ከቀኑ 7 ሰአት ከ30 ጀምሮ የጣለ ሲሆን፥ ያስከተለው ጎርፍ የመኖሪያ ቤቶችን ማፈራረሱንም ፖሊስ አስታውቋል።
በጎርፉ ሳቢያ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ የ4 አመት ህጻን እና የ2 ወር ጨቅላ ህይወታቸው አልፏል ነው ያለው።
እንዲሁም በሌላ መኖሪያ ቤት የነበሩ የ19 አመት ታዳጊ እና የ45 አመት ጎልማሳ በጎርፍ ተወስደው ህይወታቸው አልፏል።
ከዚህ ባለፈም በሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በጎርፉ ሳቢያ ከ31 በላይ ቤቶች ሲፈርሱ በርካታ ቤቶችም በጎርፍ ተጥለቅልቀው ንብረቶች ወድመዋል።
በጎርፍ የተወሰዱ 3 የባጃጅና የፎርስ ተሽከርካሪዎችም አሸዋ ውስጥ ተቀብረው መገኘታቸውንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
ጎርፉ በርካታ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ የመኖሪያና የመስሪያ ቤት አጥሮችን በማፍረስም የተለያዩ የመደብር እቃዎችን ወስዷልም ነው ያለው።
በቀጣይም ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።