አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና እና ኢትዮ ቴሌኮም የኮኔክቲቪቲ እና ዲጅታል አገልግሎቶች አቅርቦት የስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና እና የኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ተማሪያዎች በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት ክፍያዎችን በቴሌብር አማካኝነት መክፈል የሚያስችል ሲሆን ተማሪዎች በቀላሉ እና ባሉበት ቦታ ሆነው ክፍያቸውን በቴሌብር አማካኝነት ለመክፈል የሚያስችል ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደ ሃና (ፕ/ር) ÷የአንድ ሀገር እድገት የሚወሰነው ባለው የተማረ የሰው ሃይል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የተማረውን የሰው ሃይል በቴክኖሎጅ መደገፍ ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው ስምምነት ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የቴክኖሎጅ ጉዞ የሚያሳካ እና የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው ÷ ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የዛሬው ስምምነት በትምህርት ተቋማት ብቁ እና ተወዳዳሪ ለማፍራት ብሎም ችግር ፈች ምርምሮችን ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡
በሳሙኤል ወርቃየሁ