Fana: At a Speed of Life!

በደብረ-ኤሊያስ ወረዳ የተገኘው ሠላም እንዲዘልቅ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ በፀረ -ሠላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ እርምጃ የተገኘውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ምዕራብ ዕዝ 403ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ÷ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በሥላሴ ገዳም አካባቢ የመሸገው የታጠቀ ፅንፈኛ ኃይል ÷ የአካባቢውን ሕዝብ የኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ልማት አንቅስቃሴዎች ከማስተጓጎሉም በላይ የጸረ ሠላም ኃይሉን አስተሳሰብ የማይቀበሉ ግለሰቦችን ሲገድሉ እንደነበረ አስታውሰዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃም ፀረ-ሠላም ኃይሉ መመታቱን እና ተንጠባጥቦ በመሸሽ ላይ ያለውን የመከታተል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአካባቢው መስተዳድርና ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበርም የተገኘውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ ከጽንፈኛ ኃይሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሠላምና ደኅንነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ላቃቸው አብጠው ÷ በአካባቢው የተገኘውን ሠላም ለማጽናት በትኩረት እና በትብብር እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ፀረ-ሠላም ኃይሎቹ ÷ በአመለካከት የማይደግፏቸውን ንፁሃን ዜጎች፣ አመራሮችና የሃይማኖት አባቶችን ሲገድሉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ገዳሙ ትክክለኛ የኃይማኖት ሥፍራ እንዲሆን ከጠቅላይ ቤተ-ክሕነትና ከዞኑ ሀገረ ስብከት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ምስሎችን በመቆራረጥና በማገናኘት ገዳሙ እንደወደመ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ሁሉም ህዝብ ሊያውቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አሁን የተገኘውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግም ሕዝቡ ሃይማኖትን ሽፋን በማድርግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሥፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ማጋለጥና መታገል አለበት ሲሉም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.