Fana: At a Speed of Life!

ጤናማ የግብይት ሥርዓትን መተግበር የሚያስችል የታሪፍ ሥርዓት ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴሌኮም ዘርፍ ጤናማ የግብይት ሥርዓትን መተግበር የሚያስችል የታሪፍ ስርዓት ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ባልቻ ሬባ እንደገለጹት ÷ ተቋሙ በቴሌኮም ዘርፍ በውድድር ላይ የተመሰረተ ጤናማ ገበያ ለመገንባት እየሠራ ይገኛል።

ለዚህም ለቴሌኮም አገልግሎት ወጪን መሰረት ያደረገ የዋጋ መከታተያ ስርዓት መዘርጋት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

ለሞባይልም ይሁን ለመደበኛ ስልክ አገልግሎት ዋጋ በሚተመንበት ጊዜ ፤ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚወጣው ወጪ ብቻ ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታልም ብለዋል።

የሞባይል አገልግሎት ገቢን ለቋሚ አገልግሎት መደገፊያና የሞባይል የድምጽ ገቢን ለኢንተርኔት መደጎሚያ ማዋል ከተወዳዳሪነት አንጻር አይፈቀድም።

በመሆኑም ስርዓቱ መዘርጋቱ ደንበኞች ያልተጠቀሙበትን ወጪ እንዳይከፍሉ ለመከታተል ያግዛል ነው ያሉት።

ስርዓቱን ለመዘርጋት ከመሰረተ ልማት መጋራት ጋር ላይ ያለውን ትክክለኛ ዋጋ ማወቅ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጥናቱ ሙሉ ለሙሉ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተጠናቆ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራች እንደምትገኝም ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮ-ቴሌኮም 69 ሚሊየን እንዲሁም ሳፋሪኮም 3 ሚሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።

ከሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ቀጥሎ በፍጥነት እያደገ ያለው የኢንተርኔትና ዳታ አገልግሎት ሲሆን ፥ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገልግሎት ሰጪዎች ከ33 ሚሊየን በላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

የፊክስድ ብሮድ ባንድ ወይንም መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.