ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ብሪታኒያ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነታቸውን ማሳደግ በሚችሉበት አግባብ ላይ ተወያዩ፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ከብሪታኒያ ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ኒገል ሃድልስተን ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምሥጋኑ ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ ያላቸውን የረዥም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት አውስተው ግንኙነታቸውን የበለጠ ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚኒስትሩ ጋር መክረዋል።
ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየወሰደች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማብራራታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የሀገሪቷን የንግድ ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ስለላኩም አመሥግነዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ለመተባበር ያላትንም ዝግጁነት አንስተዋል።
ኒገል ሃድልስተን በበኩላቸው ÷ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ያላትን ፍላጎት አፅንዖት ሰጥተው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እያደገች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ላደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያም ያላቸውን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።