Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ቦትስዋናን የቆየ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ያለውን የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ÷ ከቦትስዋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካና መካከለኛ ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፑሌ ምፖትዌ ጋር በሀገራዊና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሙክታር (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በቀጠናዊ የንግድ ትሥሥርና ሃብቶችን ይበልጥ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ለመሥራት የሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት እና ማዕድን ሐብቶች ልማትና አጠቃቀም ዙሪያ ቦትስዋና ካላት ልምድ ለመማር እንደምትፈልግም አስረድተዋል።

ሁለቱን ሀገራት በሁሉም መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተፈረሙ ሥምምነቶችን አፈጻጸም መገምገም እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

የተጀመረው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም በሁለቱም ወገኖች በኩል ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካና መካከለኛ ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፑሌ ምፖትዌ ÷ ቦትስዋና ከኢትዮጵያም ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከአቪዬሽን እና ሆልቲካልቸር ልምዶችን ለመካፈል እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራም መገለጹን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንኑ ለማሳካት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በቅርብ ጊዜ  የሚካሄድበት ሁኔታ እንዲመቻች በሁለቱም ወገኖች በኩል ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግም ፑሌ ምፖትዌ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.