በጤና አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን አይተናል- ጎብኝዋች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤና አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን ተመልክተናል ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና ጄነራል መኮንኖች ገለጹ፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና ጄነራል መኮንኖች ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የጤና አውደ ርዕይ ሲጎበኙ በጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አማካሪ ሌተናል ጄነራል ዓለምእሸት ደግፌ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት÷ በኤግዚቢሽኑ የቀረቡት የሐገሪቱን ሕክምና ደረጃ የሚያሳይና ሌሎች ተቋማትም ልምድ የሚቀስሙበት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው፡፡
ከሀገር በቀል ሕክምና እስከ ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂ በዘርፉ ያለውን ተጨባጭ ውጤት በማየታቸው ኩራት እንደተሠማቸውም ነው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ የሕክምና መሳሪያዎች መሃንዲስ አቅርቦት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል የሺመቤት አያሌው ÷ አውደ ርዕዩ የሕክምናውን ዘርፍ የቴክኖሎጂ እድገት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ የጤና ኤግዚቢሽኑ ዋነኛ ዓላማ በዘርፉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጠፋ የጤና ስርአት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል።
በጤና ሥርዓቱ ሕብረተሰቡም የራሱን ጤና በራሱ በመጠበቅና በተለይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ጥረቱን እንዲያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።