ኢትዮጵያ በ“ሞባይል”በምታሳልጠው ግብይት ተጨማሪ 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ታገኛለች – ዓለም አቀፍ ጥናት
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2030 ከዓመታዊ የሀገር ውስጥ ገቢዋ በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ሥልክ በምታሳልጠው ግብይት 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ያኅል ገቢ እንደምታገኝ ዓለም አቀፍ ጥናት አመላከተ፡፡
በዛሬው ዕለት በተንቀሳቃሽ ሥልክ በሚከናወኑ የዲጂታል ግብይቶች ላይ ጥናት እና ምርምሮችን የሚያካሂደው በምኅፃረ-ቃል “ጂ. ኤስ. ኤም. ኤ” እየተባለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ ድርጅት ዓመታዊ ጥናቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ዓመት የጥናት ውጤቱ ይፋ እንዳደረገውም፥ በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ሥልክ ግብይት እና የዲጂታል ኢኮኖሚው የሚያንቀሳቅሰው ንዋይ እያደገ መጥቷል፡፡
ሀገሪቷ ለዲጂታሉ የግብይት ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ በመሥራት ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ግብር በተንቀሳቃሽ ሥልክ በሚፈጸም የአከፋፈል ሥርዓት እንደሚሰበሰብ ጠቁሟል፡፡
በዚህም በዘርፉ የሚሰበሰበው ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ገቢ እንደሚያድግና የሀገሪቷ ምጣኔ ሐብትም በቀላሉ በሁኔታዎች የማይበገር እንደሚሆን ከወዲሁ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በተንቀሳቃሽ ሥልክ በሚሰበሰብ ግብር ሀገሪቷ 300 ሚሊየን ዶላር ያህል ገቢ ታገኛለችም ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም በሥርዓቱ 700 ሺህ ያኀል ሰዎች ከጥልቅ የድኅነት አረንቋ እንደሚላቀቁ በጥናቱ ተገልጿል።
የ“ጂ. ኤስ. ኤም. ኤ” ጥናት፥ በፈረንጆቹ 2030 በኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ሥልክ የሚጠቀሙ ሰዎች 60 በመቶ ይደርሳሉም ብሏል።