Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለሲ ዲሲ የሚጠበቅባትን ድጋፍ ትቀጥላለች- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) የሚደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ ዲ ሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በውይይታቸው ላይ እንደገለጹት÷ ማዕከሉ የአፍሪካን የጤና አጀንዳዎች ወደ ፊት ለማራመድ እንዲያስችል ሆኖ የተገነባ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ አወድሰዋል።

ዶክተር ዣን ካሴያ በበኩላቸው÷ ማዕከሉ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ በማገዝ ረገድ ኢትዮጵያ ጉልኅ ሚና ተጫውታለች ሲሉ እውቅና ሰጥተዋል፡፡

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ እንዲቋቋም የኢትዮጵያ እገዛ ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ማዕከሉ ለአባል ሀገራቱ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እና የማማከር ተግባሩን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ከተቋቋመ ጀምሮ ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለው አስተዋፅኦም የሚደነቅ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በአኅጉሩ ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ምርምር የሚካሄድበትና እና ግኝቶች የሚወጡበት የላቦራቶሪ ሥርዓት በመገንባት ረገድም ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ ማበርከቷን ተናግረዋል፡፡

ጤናን የተመለከቱ ተቋማዊ ጉዳዮች በሥርዓት እንዲመሩ እና አፍሪካ የተሻለ የጤና አገልግሎት አማራጮች እንዲኖራት ኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ማበርከቷንም ነው የገለጹት፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.