Fana: At a Speed of Life!

ኢራን በንግዱ ዘርፍ በሦስት ዓመታት 10 ቢሊየን ዶላር በአፍሪካ የማፍሰስ ፋላጎት አሳየች

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በአፍሪካ የባሕር ላይ የንግድ ግንኙነቷን ማጠናከር እና እስከ 10 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ እንደምትፈልግ ተገለጸ፡፡

ኢራን በመርከብ የማጓጓዣ አገልግሎት ከአፍሪካ ጋር የምታካሂደውን የባሕር የንግድ ግንኙነት ይፋ ያረጉት የኢራን የንግድ ማስታወቂያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሞሐመድ ሳዴቅ ናቸው፡፡

የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌ አጭር ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገው አጠናቀዋል፡፡

ሀገራቱ ከኢራን ጋር የወሳኝ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ሥምምነቶች መፈራረማቸውን አር ኤፍ አይ ዘግቧል፡፡

የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ተከትሎ ኢራን በቀጥታ በባሕር ትራንስፖርት ከአፍሪካ ጋር የሚኖራትን የንግድ ግንኙነት ለማሳለጥ አኅጉራዊ ቢሮ ለመክፈት ማቀዷን የፋርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የሀገሪቷ የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አሚር ባያት÷ በሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ በመርከብ የቀጥታ የባሕር ማጓጓዣ አገልግሎት መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል፡፡

በቀጣይም አገልግሎታቸውን ወደ ቀሪዎቹ የአፍሪካ ቀጣናዎች ለማስፋት ዕቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ አፍሪካን “የዕድሎች አኅጉር” ብለው ሲጠሯት÷ ጉብኝታቸው በኢራን እና በአፍሪካ አኅጉር መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በር የከፈተ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.