Fana: At a Speed of Life!

ለምስራቅ አፍሪካ አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ተቋማዊ አቅም እየተፈጠረ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አገልግሎት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ማምጣት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገለፀ።

የድርጅቱ የኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋሻው ተስፋዬ ፥ ለምርትና አገልግሎቶች የፍተሻ ላቦራቶሪ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎትን ማዘመን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ በንግድ ግብዓቶች ላይ የሚኖሩ ክርክሮችን ለመዳኘት መመረጡን ጠቅሰው÷ ይህን አቅም በማጠናከር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ተቋም ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስፈትሹ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘባቸው 145 የፍተሻ ላቦራቶሪ፣ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ወሰኖች÷ በ2015 ዓ.ም ለ22 ሺህ 334 አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አገልግሎቶች ጅቡቲን ጨምሮ በአዲስ አበባና በክልል በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እየሰጠ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

በድርጅቱ የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የእውቅና ማረጋገጫ አግኝተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.