በየቀኑ በአማካኝ 20 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተሰራጨ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ በአማካኝ 20 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተሰራጨ እንደሆነ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
ከጅቡቲ ወደብ በባቡር ተጓጉዞ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያበፍጥነት ወደ ማሰራጫ ማዕከሎች እንዲደርስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አመላክቷል።
በዚህም በየቀኑ በአማካይ እስከ 20 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሰራጨ እንደሆነ ጠቁሟል።
በእንዶዴ ባቡር ጣቢያ ተገኝተው በባቡር ተጓጉዞ የሚመጣው የአፈር ማዳበሪያ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሰራጭበትን ሂደት የተመለከሩት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ፥ የባቡር ምልልስን በመጨመር የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ አቅምን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የጭነት ተሽከርካሪዎች በባቡር ጣቢያ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ በማድረግ የሚደርሰውን የአፈር ማዳበሪያ በአጭር ጊዜ ለማሰራጨት እየተሰራ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
ሰሞኑን የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ ሂደት የታየው የመፈፀም አቅም በቀጣይ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን ለማሳደግ ለሚሰሩ ስራዎች ትምህርት እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት።
ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀናጅተው በትጋት መስራታቸው ውጤት አስገኝቷልም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአፈር ማዳደሪያ ተጓጉዞ እስከሚያልቅ ድረስ በከፍተኛ ክትትል የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በሙሉ አቅም መስራት እንደሚገባ ማመልከታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።