Fana: At a Speed of Life!

በክረምቱ በድልድዮች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ አሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ232 ሚሊየን ብር ወጪ በተለያዩ አካባቢዎች ፈርሰው የነበሩ ድልድችን በመገንባትእና በመጠገን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡

በአስተዳደሩ የድልድይ እና ስትራክቸር ስራዎች ዳይሬክተር ጌትነት ዘለቀ (ኢ/ር) እንደገለጹት÷ በ2015 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች የፈረሱ ድልድዮች ለትራንስፖርት መሳለጥ ተግዳሮች ፈጥረው ነበር፡፡

በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ድልድዮችን በመገንባት እና በመጠገን አገልግሎት ለማስጀመር አስፈላጊው ርብርብ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢወች በጎርፍ አደጋ ፣ በከፍተኛ ክብደት እና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ ፈርሰው የነበሩ ድልድዮችን በመገንባት አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሰረት በጀማ፣ ጺላሪ፣ አለውሃ፣ ተከዜ፣ አደሃ፣ ገራግሌ፣ በኬ፣ ቻርግ፣ ጂማ፣ ጎቡና በሌሎች ወንዞች ላይ ፈርሰው የነበሩ ድልድዮች ተገንብተው ዳግም አገልግሎት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡

ለዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታቸው የተጠናቀቁትን ጨምሮ ከ232 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡

እያንዳንዱ ድልድይ ከ40 ቶን በላይ ክብደት መሸከም አይችልም ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ችግሩን ለመቀነስ አሽከርካሪዎች ድልድዮች ላይ ተጠባብቀው በማለፍ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት እንዲቀንሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.