በአማራ ክልል 668 ከተሞች በመዋቅራዊ ፕላን እየተመሩ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል 668 ከተሞች በፕላን የሚመሩ እንዲሆኑ መደረጉን የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በአማራ ክልል ከሚገኙ 683 ከተሞች ውስጥ 668 ከተሞች በፕላን የሚመሩ ከተሞች እንዲሆኑ ተደርጓል።
አንድን ከተማ፤ ከተማ የሚያሰኘው በፕላን መመራቱ ነው ያሉት ሀላፊው÷ የከተሞችን ፕላን መነሻ በማድረግ ሌሎች የከተማ ልማት ስራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከተሞችን በፕላን መምራት ከተሞቹ ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል፡፡
የከተማ ፕላን አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ የሚያበቃ አለመሆኑን በመጥቀስም እንደየከተሞቹ ባህሪ በ10 አመት ወይም በ20 አመት እንደሚከለስም አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በክልሉ የባህር ዳር ከተማን የ30 አመት እጣ ፋንታ እንዲወስን ተደርጎ ካለፈው አመት ጀምሮ የተተገበረ መዋቅራዊ ፕላን ተጠናቆ ወደ ትግበራ መገባቱን አስታውሰዋል፡፡
በተለይ የትላልቅ ከተሞች ፕላን ሲዘጋጅ የሌሎች ሀገራትን እንዲሁም በኢትዮጵያ የተሻሉ ከተሞችን ተሞክሮ ተወስዶ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም ከተሞች ፕላናቸውን ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸው÷ የከተማ ፕላን ትግበራ ሂደትን የሚፈታተኑ ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
ሕገ ወጥ ግንባታዎች፣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዲሁም ከግንባታ ዲዛይን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች የከተማ ፕላን ተግባራዊ እንዳይሆን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡
ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሮች የሚፈቱበትን አሰራር በመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝም ሀላፊው አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል አዳዲስ ፕላን ያልተሰራላቸው ከተሞችን በማጠናቀቅ ፕላን የሌለው ከተማ በክልሉ እንዳይኖር ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቅሰው÷የከተማ ፕላን በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ አሳስበዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት