Fana: At a Speed of Life!

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን ለመከላከል ባለድርሻዎችን የሚያቀናጅ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለወንጀል ተጋላጭ እያደረገ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሰው መነገድና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በተዘጋጀ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው፥ በሰው መነገድ፣ በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ወደ ውጭ ለስራ ስምሪት መላክ ዜጎችን ለወንጀል ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው ብለዋል።

በተለይ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት የሚጓዙ ዜጎች ለሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ተጋላጭ በመሆናቸው ለአካላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃት ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አመልክተዋል።

ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀና አድማሱን እያሰፋ መምጣቱን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው÷በፍጥነቱ ልክ ተጠያቂነትን በማስፈንና ቅንጅታዊ አሰራርን በመተግብር ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም የፍትሕ ሚኒስቴር ከሌሎች ተቋማት ጋር “ሀገር አቀፍ የሰው መነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂ” ማዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

የስትራቴጂው ይዘት ቀርቦ ከባለድርሻ አካላቱ ግብዓት የተሰጠበት ሲሆን÷ ረቂቁ ፀድቆ ወደ ትግበራ ሲገባ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት ለችግሩ መፍትሄ ያመጣል የሚል ዕምነት ተጥሎበታል።

በመድረኩ የፌዴራል እና የክልል የፍትሕ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.