በኦሮሚያ ክልል ከ3 ሚሊየን በላይ የሻይ ቅጠል ተክል እየለማ መሆኑ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቭ እስካሁን ከ200 ሄክታር በሚበልጥ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ከ3 ሚሊየን በላይ የሻይ ቅጠል ተክል እየለማ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
በ2015 ዓ.ም ከተዘጋጀው ከ4 ሚሊየን በላይ የሻይ ቅጠል ተክል ውስጥ እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህሉ መተከሉን አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
የሻይ ቅጠል ልማት ለአርሶአደሩም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከሚያበረክቱ የኤክስፖርት ምርቶች አንዱ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ይህን በመረዳትም የሻይ ቅጠል ልማት ኢኒሼቲቭ በ2014 ዓ.ም “የአሌ የሻይ ቅጠል ልማት ዲክላሬሽን” መታወጁን ነው ያስታወሱት፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሻይ ቅጠል ምርት በኢሉአባ ቦራ ዞን አሌ ወረዳ ብቻ ሲለማ መቆየቱን ጠቁመው÷ አሁን ወደ ጅማ፣ ቡኖ በደሌ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ማስፋፋት ተችሏል ብለዋል፡፡
እስካሁን ከተተከሉት ተክሎች ከሦስት ዓመታት በኋላ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀመርም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህም ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያሳድግ ነው አቶ ሽመልስ የገለጹት፡፡
ለወደፊቱም ይህንን ስራ የበለጠ ለማስፋፋት የሻይ ቅጠል ተክሎች ዝግጅት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡