Fana: At a Speed of Life!

ከ82 ሚሊየን ብር በላይ ግብርና ታክስ በማሳጣት በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተከሳሽ ጥፋተኛ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ82 ሚሊየን ብር በላይ ግብርና ታክስ በማሳጣት በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሷል የተባለው ተከሳሽ ጥፋተኛ ተባለ።

የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ ሰለሞን ገ/እግዛብሔር አፅብሃ ሲሆን÷ የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦበታል።

ተከሳሹ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነሃሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ተረጋግጦ እንደተሰጠ የሚገልጽ ቢኒያም አድማሱ በሚል አየለች ሙሉነህ አበራ ለተባለች ግለሰብ የተሰጠ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በመጠቀም የተጨማሪ እሴት ታክስ እጅ በእጅ ደረሰኝ ህትመት ፈቃድ በመውሰድ ከጁፒተር ንግድ ስራ ኃ/የተ የግ/ማህበር ጋር እና ከሀሮን ኮምፒዩተር ስራ ኃ/የተ የግ/ማህበር ጋር በመዋዋል የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በመውሰድ በሌላ ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር መጠቀሙ በክሱ ተዘርዝሯል።

በሌላ ክስም ተከሳሹ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በግብር ከፋይነት በተመዘገበች ግለሰብ ስም ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ ተረጋግጦ እንደተሰጠ የሚገልጽ መታወቂያ በመጠቀም የንግድ ስራ በመስራት 77 ሚሊየን 232 ሺህ 275 ብር ከ98 ሳንቲም ግብርና ታክስ እንዲጭበረበር በማድረግ እንዲሁም በሌላ ሰው ስም ንግድ ስራ መስራት ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

በተጨማሪም ተከሳሹ በግብር ከፋይ መለያ የተመዘገበች አመለ አድማሱ በተባለች ግለሰብ ስም ደግሞ ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም በፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ ተረጋግጦ እንደተሰጠ የሚገልጽ ሀሰተኛ የውክልና ማስረጃ በመጠቀም እንዲሁም ቢኒያም አድማሱ ቦጋለ በሚል ሀሰተኛ ማንነት ተጠቅሞ ባወጣው ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመጠቀም የንግድ ስራ በመስራት 4 ሚሊየን 993 ሺህ 761 ብር ከ36 ሳንቲም እንዲጭበረበር በማድረግ በሌላ ሰው ስም የንግድ ስራ መስራት ወንጀል መከሰሱም በዝርዝር ቀርቧል።

በተጨማሪም ተከሳሹ የንግድ ስራ አዋጅ ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጽ/ቤት እንደተሰጠ የሚገልጽ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመያዝ ተከሳሹ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ ተረጋግጦ እንደተሰጠ የሚገልጽ ከሰለሞን ገ/እግዛብሔር ለቢኒያም አድማሱ የሚል ሀሰተኛ የውክልና ማስረጃን መገልገሉ ተጠቅሷል፡፡

በዚሁ ሀሰተኛ ማስረጃ በስሙ ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ንግድ ጽ/ቤት ቢሮ የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ እና የኮንስትራክሽን ንግድ ፈቃድ በማውጣት ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም በሀሰተኛ ሰነድ የንግድ ፈቃድ ማውጣቱ ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሹ የቀረበበትን ተደራራቢ ክስ በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ከስምንት በላይ የሰው ምስክሮችን እና የተያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦበታል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል በሰጠው ብይን መሰረት በተገቢ መልኩ መከላከል አለመቻሉ ተጠቅሶ በዛሬው ቀጠሮ ተብራርቷል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።

የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ለመጠባበቅ እና ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.