Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት ይሰራል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በክልሉ የታጠቁ ሃይላት የመንግስትን ሰላማዊ ጥሪ ባለመቀበል ግጭት መፍጠራቸውን እና ይህንንም በክልሉ የፀጥታ መዋቅር መፍታት ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተናግረዋል።

 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የክልሉን ሙሉ ሰላም ማረጋገጥ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

 

በክልሉ ፅንፈኛ ሀይሎች ግጭት በመፍጠር ዘረፋና ህዝቡን ወዳልተገባ ሁኔታ እያስገቡ መሆኑንም አንስተዋል።

 

የፀጥታ መዋቅሩ በነፃነት ተንቀሳቅሶ ህግ እንዳያስከብር ህፃናትን ከፊት በማሰለፍ የክልሉን ሰላም ማደፍረስ ላይ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።

 

ወቅቱ የመኽር አዝመራ የሚዘራበት እንደመሆኑ ለአርሶአደሩ የሚላከውን የአፈር ማዳበሪያ እየዘረፈ አርሶአደሩን እያጉላላ ይገኛል ብለዋል።

 

በክልሉ ለእነዚህ ሀይላት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢደረግላቸውም የሰላም ጥሪውን ከመቀበል ይልቅ አመራሮችን መግደልና ግጭት መፍጠርን ምርጫቸው አድርገዋልም ነው ያሉት።

 

መንግስት ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ሲመለከተው የቆየ ቢሆንም እየሰፋና ሁኔታውም ለሌሎች ሀይሎች ጣልቃ መግባት እድል የሚሰጥ በመሆኑ ህግ ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ መገደዱን አስታውሰዋል።

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሚያፀድቀው ድረስ የሚያስተገብር ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተደራጅቶ ስራ መጀመሩንም አንስተዋል።

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በቀናቶች ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተሰብስበው እንደሚያፀድቁት ገልፀዋል።

 

ክልሉ ወደነበረበት ሰላም እንዲመለስና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲተገበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

 

በታሪኩ ለገሰ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.