የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው የአማራ ከልል አካባቢዎች የተቋማት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው የአማራ ከልል አካባቢዎች የአገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እየተመለሰ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ በወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራት መገምገሙን አስታውሰዋል፡፡
ዕዙ በመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅዱ በባህርዳር፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋሮቢት ከተሞች የተሰባሰበውን ዘራፊ እና አጥፊ ቡድን በመምታት አካባቢዎቹ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በስድስቱም ከተሞች ውስጥ እና ዙሪያ የተሰገሰገው ሃይል መሳሪያ እንዲያስረክብ እና እጁን ለፀጥታ ሃይሎች እንዲሰጥ የተሰጠውን እድል ባለመጠቀሙም እርምጃ ተወስዶበታል ነው ያሉት፡፡
የህግ የበይላነት እንዲከበር መደረጉንም ነው ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)የገለፁት፡፡
ለዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ የህግ አስከባሪዎቹ ተልዕኮአቸውን እንዲወጡ እገዛ ማድረጉን ገልፀው፤ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ እዙ ምስጋና እንዳለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም አካባቢዎቹ ከዚህ ዘራፊ መንጋ ስጋት ነፃ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የመከላከያ ሰራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት በየስርቻው ተራረፈውን ፅንፈኛ ኃይል በማፅዳት ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ አድርጓል ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡም ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ አካባቢውን ከዘረፊ በመጠበቅ፣ የተዘጉ መንገዶችን በራሱ አቅም በማስከፈት የወደሙ እና የተዘረፉ ንብረቶችን ለመለየት እና ለየባለቤቶቹ እንዲመለሱ ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሰላም እንዲረጋገጥም ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡
ባህርዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻ ለጊዜው ተቋርጦ የነበረው በረራ መጀመሩን አመላክተዋል፡፡
በስድስቱም ከተሞች የግል እና የመንግስት አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተው በዚህም በአብዛኞቹ ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው