Fana: At a Speed of Life!

የመካከለኛው የምግብ እጥረት ህክምናን ወደ ጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ለማስገባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመካከለኛው የምግብ እጥረት ህክምናን ወደ ጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ።

 

ስምምነቱ በጤና ሚኒስቴር፣ በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት የተፈረመ ነው።

 

በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ካለፉት ዓመታት ወዲህ በተሰሩ ስራዎች በኢትዮጵያ በጨቅላ ህፃናት ላይ የሚስተዋለው የመቀንጨር እና የመቀጨጭ ችግር መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል።

 

የተስተዋሉ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ላይ እንቅፋት መፍጠራቸውን በመጥቀስ፥ ይህም በተለይ በልጃገረዶች፣ በአጥቢ እናቶች፣ በጨቅላ ህፃናትና፣ በነፍሰጡር እናቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማስከተሉን አንስተዋል።

 

በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጄኒፈር ቢቶንድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ እጥረትን ለመከላከልና በምግብ እጥረት ምክንያት ለሚፈጠሩ የጤናና ተያያዥ እክሎች እየሰጠ ያለውን አፋጣኝ ምላሽ አድንቀዋል።

 

በዚህም የመቀንጨር ምጣኔን ከ58 በመቶ ወደ 37 በመቶ እንዲሁም መቀጨጭን ከ10 በመቶ ወደ 7 በመቶ መቀነስ እንደተቻለ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

 

የምግብ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ እና የተያዘውን ግብ ለማሳካት በዘርፉ የተገኘውን ሀብት በአግባቡ መያዝ እና ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እና በትብብር መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.