የብሩህ አይሲቲ ውድድር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ብሩህ አይሲቲ የስራ ሀሳብ ውድድር በዛሬው እለት ተጠናቋል።
ውድድሩ ከመላ ሀገሪቱ የተሰባሰቡ ወጣቶች ቢሾፍቱ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት የቢዝነስ አመራርን ጨምሮ የተለያዩ ጠቃሚ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በማጠናቀቂያ መድረኩ እንዳሉት ÷ የተለያዩ ሀገራዊ ፀጋዎችን በመለየት የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
የስራ ሀሳብ ያላቸውን አሰልጥኖ በማወዳደር ለሽልማት ማብቃት ላይ መሰራት እንዳለበት ገልጸው፤ በሀገራችን ያሉ ስራ ፈጣሪዎች ምቹ መንገድ እንዲፈጠርላቸው እየተደረገ ነው ብለዋል።
እንዲህ አይነቱ ውድድር ቀጣይነት እንደሚኖረው የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ባለሀብቶች ከእነዚህ የስራ ሀሳብ አመንጪዎች ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አስር ስራ ፈጣሪዎች 260 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በታምሩ ከፈለኝ