የተመረቁት ኮማንዶዎች ሁለት ዓላማ አላቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ አስቸጋሪ መሰናክሎችን ማለፍን እንዲሁም ፈጥኖ መድረስን ለሚጠይቁ ተልዕኮዎች ጠንካራ ስልጠና ወስደው የተመረቁ ኮማንዶዎች ሁለት ዓላማ እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ ጠዋት የኢትዮጵያ ትልቁ ኤሊት ኃይል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘቴ ክብር ይሰማኛል” ብለዋል።
በመልዕክታቸውም ይህ ኃይል ሁለት ዓላማዎች አሉት በማለት ገልጸው፤ ውጊያ ማስቀረት እና ገፍቶ ከመጣ ደግሞ ውጊያን የመጨረስ ተልዕኮ ያለው ነው ሲሉ ዓላማውን አስረድተዋል።
እንዲህ ያለው ኃይል ይህቺን ትልቅ ሀገር አጽንቶ ለትውልድ ያሻግራል ብለዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የተወጣጣ ኅብረ ብሄራዊ ሠራዊት እየገነባን ነው ብለዋል፡፡
እየሠራን ያለነው ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል ብቃት ያለው ሠራዊት እያበቃን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
የብላቴ ኮማንዶና የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ኮማንዶዎችን ዛሬ ማስመረቁ ይታወቃል።