የሚቀጥሉት 10 ቀናት የዝናብ መጠን ለመኸር ሰብሎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ በተለያዩ የእድገት ደረጃ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎች እድገት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ፥ በቀጣዩቹ 10 ቀናት የመኸር ሰብል አምራች በሆኑትም ሆነ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ቀጣይነት ያለው የእርጥበት ሥርጭት ሊኖር እንደሚችል ትንበያው አስታውቋል።
ይህም እርጥበት በተለያዩ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
በተለይ የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻሉ በተጨማሪ በአንዳንድ እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የዝናብ ውሃን ለማሰባሰብ እገዛ እንደሚያደርግም ነው ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ያመላከተው።
በአንዳንድ የምስራቅና የደቡባዊ ክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች በመጠን ዝቅተኛ የሆነ እርጥበት የሚጠበቅ በመሆኑ በእነዚህ ቦታዎች የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲልም አብራርቷል።
በሌላ በኩል ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው የሰሜንና የምዕራብ አጋማሽ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ በማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ ከወዲሁ መዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነም ነው የተጠቆመው፡፡
ከእርጥበት መብዛት የተነሳ የአረም መስፋፋትም ሆነ ለሰብል በሽታዎችና ተባዮች መከሰት ምቹ ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል አርሶ አደሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ትንበያው አመልክቷል።
በአጠቃላይ የዝናብ መጠን ከፍተኛ በሆኑ አካባቢ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጎርፍ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ነው ኢንስቲትዩቱ ያስገነዘበው፡፡