የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ እንደገለጹት÷ጠንካራ የአቅርቦትና ግብይት ሰንሰለት በመፍጠር ጥራታቸውን የጠበቁ ግብዓቶችን በማቅረብ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ድርጅቱ መንግስት ቅድሚያ በሰጣቸው ዘርፎች ለተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃና የተለያዩ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚችልበት አቅም ለመፍጠር ድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ቫይታሚን የምግብ ማቀነባበሪያ፣ የኢንዱስትሪ ጨው፣ ኖዱልስ የሳሙና ጥሬ እቃ፣ የመድሃኒት እና ሌሎች ግብዓቶችን ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በገበያ ላይ እጥረት የሚስተዋልባቸው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጠኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም ከኢንዱስትሪ ግብዓቶችና ውጤቶች ሽያጭ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች 4 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ወ/ሮ የሺመቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ቀልጣፋና ውጤታማ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የአቅርቦት ሰንሰለት አሰራርን ለመተግበር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉት ቅርንጫፎች ራሳቸውን ችለው ገዝተው መሸጥ የሚችሉበትን አቅም ማጠናከር ላይ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ