ስድስት የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ስድስት የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊው ሒደት መጀመሩን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው÷በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለመስሕብነት ለማዋል እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረት አዳዲስ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች ተጨማሪ የቱሪዝም መስሕብ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ዓመትም ጮቄ ተራራ እና ወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይም በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በጥናት የመለየት እና መረጃ የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ቦታዎችም በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች እንደሚገኙ ነው አቶ አለማየሁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙም አስፈላጊው መረጃ ለድርጅቱ መላኩን አንስተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ