Fana: At a Speed of Life!

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝቡን እንካስ – አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ የሕዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝቡን እንካስ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር በዓለ ሲመት መልእክት ያስተላለፉት አፈ ጉባዔዋ ፥ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ምሥጋና አቅርበዋል።

የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ሀገር የገነባ፣ ከሁሉም ጋር የተዋለደና የተጋመደ፣ ፍትሕን የሚሻና ለማግኘት የሚተጋ፣ ሀገር ወዳድ ታታሪና አቃፊ ሕዝብ ነው ብለዋል በመልእክታቸው።

ባለፉት ዓመታት የተዘራው ሐሰተኛ ትርክት የአማራን ሕዝብ የሚገልጽ እንዳልሆነ ገልጸው ፥ በዚህ ምክንያትም ክልሉ ሕዝብ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ቆይቷልም ብለዋል።

በዚህም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝቡን እንድንክስ እጠይቃለሁ ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት የአማራን ሕዝብ የማይወክል ሕዝቡን ያጎሳቆለ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሰላም እጦቱ ሕዝቡን እፎይ ብሎ ወደ ሥራ እንዳይገባ እንዳደረገው ተናግረውም ፥ ሕዝቡ የሰጠንን ኃላፊነት በመወጣት ሰላምን ማረጋገጥ ትንሹ ኃላፊነት መሆኑንም ነው ያነሱት።

ያለ አግባብ ትንኮሳዎችን እና የፖለቲካ ሴራዎችን በግልፅ በመታገል ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለማጽናት አደራ ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ውለታን የማይዘነጋ ፅኑ ሕዝብ መሆኑን ገልጸውም ፥ የአማራ ሕዝብ ለእውነት ግንባሩ የማይታጠፍ ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።

ሕዝቡን ካስተባበርነው ከገጠመን ችግር በቀላሉ መውጣት ይቻላል ያሉት አፈ ጉባዔ ፥ አሁን ላይ ከፍተኛ የሀገር ኃላፊነት የምንሰጥበት ጊዜ ነውም ብለዋል።

አዲስ የተሾሙትን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እናግዝ ሲሉም አደራ ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የክልሉ ሕዝብም አዲስ ለተሾሙት መሪዎች በሙሉ ልብ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

#Ethiopia #Amhara #Ethiopianregions

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.