የሃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የ3 ቢሊየን ብር መልሶ ግንባታ ስራ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል የ3 ቢሊየን ብር መልሶ ግንባታ እና ጥገና ስራ ይፋ አድርጓል፡፡
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮፖሬት እንደገለጹት ÷ የሃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ በሆኑ ደንበኞች ላይ የሚደርስን የሃይል መቆራረጥ ችግር መፍታት የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡፡
በዚህ መሰረትም ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰትን የሃይል መቆራረጥ ለማስቀረት በ3 ቢሊየን ብር ወጪ የመልሶ ግንባታ እና ጥገና ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡
በመልሶ ግንባታው እና ጥገናው ለሃይል መቆራረጥ መንስዔ የነበሩ የተለያዩ ችግሮችን በቅደም ተከትል ለማስተካከል ከታችኛው መዋቅር ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥጋር በተገናኘ ለሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች መፍትሔ ለመስጠትም ጥናት ተካሂዶ አዲስ አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ