Fana: At a Speed of Life!

ነገ ለአትሌቶች አቀባበል ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አቀባበል ሲባል ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት ከጠዋቱ 1፡ 00 ጀምሮ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከሚያርፉበት ሒልተን ሆቴል ድረስ ደማቅ የአቀባበል ስነ-ስርዓት እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቅዱስ እስጢፋኖስ ወደ አራት ኪሎ፣ ከራስ መኮንን ድልድይ በደጎል አደባባይ ወደ ቸርችል ጎዳና፣ ከድላችን ሀውልት በአምባሳደር ወደ መስቀል አደባባይ ከዚያም በሚያርፉበት ሒልተን ሆቴል አካባቢ ለተወሰነ ሰዓት መንገዱ ለትራፊክ ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

አሽከርካሪዎችም ይህንን በመገንዘብ በቦታው ላይ የሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላትን መረጃ በመጠየቅና ተባባሪ በመሆን ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.