በዓለም የእናቶችን ቀን ታስቦ ውሏል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የእናቶች ቀን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዛሬው ዕለት ታስቦ ውሏል።
ሰዎች ስለእናታቸው ያላቸውን ፍቅር ፣ ክብር እና በእናትነቷ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ምስጋና የሚቀርብበት የእናቶች ቀን ከፈረንጆቹ 1908 ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
የእናቶች ቀን ለበርካታ ዓመታት የፈረንጆቹ ግንቦት ወር በገባ በሁለተኛ ሳምንት እሁድ እየተከበረ በዛሬው ዕለት ደርሷል።
ይህንን የእናቶች ቀንም አሜሪካ ፣ ካናዳ ፣ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት፣ አውስትራሊያ ፣ ህንድ ፣ ጃፓን እና ቻይና ግንቦታ ወር በገባ ሁለተኛው እሁድ በደማቅ ሁኔታ የሚያከብሩ ሀገራት ናቸው።
የእናቶች ቀን በአሜሪካዊቷ አና ጃርቪስ መከበር መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የእናቶች ቀን መከበር መስራች የሆንቸው የአና ጃርቪስ እናት በህይወት እያለች እንደዚህ አይነት ቀን እንዲከበር ፍላጎት እንዳላት ለልጇ ገልፃላት ነበር።
አና ጃርቪስም እናቷ በሞት ከተለየቻት በኋላ የእናትን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር ይህን የእናቶች ቀን ማክበር የጀመረች ሲሆን አለምም ይህንን ቀን ለእናት ያላትን ፍቅር እና ክብር የምትገልፅበት ሆኖ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያዊያንም ይህን ዕለት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በማህበራዊ መገነኛ ብዙሃን ለእናቶቻቸው ፍቅራቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል።