በተያዘው ክረምት ከ4 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ተደርጓል – ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው ክረምት እስካሁን ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ መደረጉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም÷ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ ባለፈው ወር ከመንግስት መጠባበቂያ ሃብት ለ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች የሚሆን የሰብዓዊ ድጋፍ መላኩን ተናግረዋል።
የሰብዓዊ ድጋፉ ከዚህ በፊት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የፋይናንስ ድጋፍ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚያቀርቡ አጋሮች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ጭምር በመድረስ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታትም ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፎችን ወደ ክልሎች ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፉ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆናል ነው ያሉት።