በመኸር ምርት ለአኩሪአተር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው – የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015/16 የምርት ዘመን መንግስት ለአኩሪአተር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)÷አኩሪአተር ለሀገር ውስጥ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ በተለይም ለዘይት ምርት አንዱ ግብዓት መሆኑን እና ለእንስሳት መኖ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ተናግረው ከዚህም የተነሳ የአኩሪ አተር ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዘንድሮ 900 ሺህ ሄክታር መሬትን በአኩሪ አተር ዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ እና እስካሁንም 705 ሺህ ሄክታር የሚሆነዉ መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በዘር የመሸፈን ስራው በቀሪዎቹ ጊዜያትም የሚቀጥል እንደሚሆንና የሚሸፈነው ሄክታር መሬትም ከፍ እንደሚል የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው መለሰ መኮንን (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ምርቱ በዉጭ ንግድም ተጨማሪ ገቢ የሚፈጠርበት ተፈላጊ በመሆኑ በከፍትኛ ትኩረት ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከአዝርዕት ሰብሎች ባለፈ የሆርቲካልቸር ሰብሎችንም ማልማት የ2015/16 የምርት ዘመን የመንግስት ከፍተኛ ትኩረቶች ናቸዉ ሲሉ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በአትክልት ፣ ፍራፍሬ ፣ ስራስር እና አበባ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ እየተሰሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዉ እስካሁን 390 ሺህ ሄክታር መሬት በሆርቲካልቸር ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ ዓመት የተሻሉ አፈፃሞች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ለዚህም የፍራፍሬ ምርቶችን በክላስተር የማምረት ስራዎቸ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በፀጋዬ ወንድወሰን