Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዩ አንድ ወር የሚኖረው እርጥበታማ አየር  ለግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዩ አንድ ወር የሚኖረው እርጥበታማ አየር  ለግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ÷በቀጣዩ አንድ ወር የሰሜን ምዕራብ፣ የምዕራብና የመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብሏል።

የአየር ሁኔታው በቀጣይ ለሚከናወኑት የግብርና እንቅስቃሴ በተለይም ዘግይተው ለተዘሩና በእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙም ሆነ ፍሬ በመሙላት ላይ ላሉት ሰብሎች ጠቃሚ መሆኑን ገልጿል፡፡

የዝናቡ ሁኔታ ለቋሚ ተክሎችም የውሃ አቅርቦት የሚረዳ ሲሆን÷ በክረምት ወቅት መጨረሻ በደጋማው አካባቢ ለሚዘሩ የጥራጥሬ ሰብሎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለዕጽዋት ልምላሜና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል የሚያግዝ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

በተለይም ባለፉት የክረምት ወራት በመደበኛ ሁኔታ ደረቅ ሆነው በሰነበቱና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት የደቡብ ኦሮሚያና የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል።

በሌላ በኩል ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚጠበቅባቸው በአንዳንድ ቦታዎች እርጥበቱ ከመጠን በላይ  ሊሆን ስለሚችልም በዚህ ሳቢያ ማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ ቦይ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.