1 ሺህ 900 ዓመታትን ያስቆጠሩ የጥንት ሮማውያን ወታደሮች መገልገያ ቁሶች በእስራኤል ተገኙ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሺህ 900 ዓመታትን ያስቆጠሩ የጥንት ሮማውያን ወታደሮች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሶች በእስራኤል ዋሻዎች መገኘታቸው ተገለፀ፡፡
የእስራኤል ጥንታዊ ቅርሶች ባለሥልጣን እንዳስታወቀው÷ አርኪኦሎጂስቶች በእስራኤል ሙት ባህር ዳርቻ አካባቢ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ባደረጉት ፍለጋ የጥንት ሮማውያን ወታደሮች መገልገያ ጎራዴ እና ፒለም የተባለ መሳሪያ ተገኝቷል፡፡
ኢን ጌዲ በተባለው የተፈጥሮ ጥብቅ ስፍራ የተገኙት ጥንታዊ ጎራዴዎች በእንጨት እና በቆዳ ቅርፊቶች ተጠቅልለው ለ1 ሺህ 900 ዓመታት መቆየታቸው ተገልጿል፡፡
የይሁዳ በረሃ ጥናት ፕሮጀክት ዳይሬክተር ኢታን ክላይ÷ መሣሪያዎቹ በወቅቱ በነበረው ጦርነት የአይሁድ ወታደሮች ከሮማውያን ወታደሮች በምርኮ መውሰዳቸውን እና ከዛም ዋሻ ውስጥ እንደደበቋቸው መላምቱን አስቀምጧል፡፡
መሳሪያዎቹ ኤን ጌዲ በተባለው የተፈጥሮ ጥብቅ ስፍራ ውስጥ በሚገኝ ዋሻ መገኘታቸው ለዚህ ማስረጃ ነው ይላሉ ኢታን ክላይ፡፡
የጦር መሳሪያዎቹ በማን፣ የትና መቼ እንደተመረቱ ለማወቅ በዋሻው ውስጥ በተገኘው የጎራዴዎቹ ሰገባዎች ላይ ተጨማሪ ምርምራ እየተደረገ ነው መባሉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡