ሀሰተኛ ገንዘብ አትመው በማሰራጨት የተጠረጠሩ 4 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሀሰተኛ ገንዘብ በማተም ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ባደረገው ክትትል በሕገ ወጥ መንገድ ሊዟዟር የነበረ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ መያዙ ተገልጿል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለቱ የውጭ ሀገራት ዜጎች ሲሆኑ÷ ሁለቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
በተደረገ ተጨማሪ ምርመራም በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አጃምባ የጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ በሕትመት ሒደት ያለ በርካታ ሀሰተኛ ብር መያዙ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተለየዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ የፎቶ ካሜራ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ላፕቶፕ እና ሌሎች እቃዎች መያዛቸው ተጠቅሷል፡፡
ከእነዚህ ማስረጃዎች በተጨማሪ ሀሰተኛ ገንዘብ ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ መያዙን የፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎች ብር እናባዛለን በሚል ከግለሰቦች ላይ ገንዘብ ሲቀበሉ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡም ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ፊጋ ተብሎ ከሚጠራበት አካባቢ ሀሰተኛ ብርና የውጪ ሀገር የገንዘብ ኖቶችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሊያዙ የቻሉት የግለሰብ መኖሪያ ቤት በመከራየት ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት እንደሚያዘጋጁ የአካባቢ ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ የሀገር መከላከያ ፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክፍለ ከተማው ሰላምና ፀጥታ በጋራ በተሰራ ስራ ነው፡፡
በዚህም በተጠርጣዎቹ የተዘጋጀ 14 ሺህ ሀሰተኛ የ200 የብር ኖት እና 250 ሺህ የተዘጋጀ ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም ከ2ሚሊየን በላይ ተቆራርጦ የተዘጋጀ ወረቀት እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡
የፀጥታ አካላቱ ሶስት ተጠርጣሪዎችን በመያዝ በጋራ ባደረጉት ክትትል ሌሎች ሶስት አባሪዎቻቸውን በአጠቃላይ ስድስት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ይዘዋል፡፡
ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ለማዘጋጀት ሲጠቀሙበት የነበረ አንድ ማሽን እና ፈሳሽ ኬሚካል እንዲሁም በገንዘቦቹ መጠን ተቆርጠው የተዘጋጁ ወረቀቶች መገኘታቸወን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡