ብሔራዊ የሠራተኞች ዲጂታል መታወቂያ በመንግሥት ተቋማት ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የሠራተኞች ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ሥራውን በጋራ ለማከናወን መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የቴክኒካል ዳይሬክተር ኢዮብ ዓለሙ እንዳሉት÷ የዲጂታል መታወቂያ የመንግሥት ተቋማት የሰው ሃብት አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን እና ለመንግሥት ውሳኔዎች መረጃ ለማደራጀት ያግዛል፡፡
እንዲሁም ወጥ የሆነ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራሙ የአሠራር ክፍተቶችን እንደሚቀንስ አንስተው÷ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ አገልግሎትን ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የመንግስት ሠራተኞችን ሠነዶች ትክክለኝነት እና ተዓማኒነት በማረጋገጥ ረገድም ሚናው የላቀ ነው ብለዋል፡፡
የኮሚሽኑ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ እና የመረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ይርጋ (ዶ/ር)÷ ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ በብሔራዊ ቋት በመመዝገብ ሠራተኞቹ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።
የሠራተኛ ቁጥርን በአግባቡ ለማወቅና ቀልጣፋ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡