ማህበሩ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓቶችን ለሆስፒታሎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓቶችን በሀገሪቱ ለሚገኙ 54 ሆስፒታሎች በማሰራጨቱን የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር አስታወቀ።
ማህበሩ 28ኛ አመት የምስረታ በዓሉን በሀዋሳ ለማክበር ይዞት የነበረውን በጀት ነው ለኮሮና መከላከል ግብዓቶች ያዋለው።
የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር የሽጥላ ተስፋዬ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ መሉ ለሙሉ ገላን የሚያለብሱ አልባሳትና ንፅህና መጠበቂያዎች በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ 54 ሆስፒታሎች ይደረጋሉ።
ቁሳቁሶቹ በሆስፒታሎች ለሚገኙ አዋላጅ ነርሶች እንደሚውሉ የተገለፀ ሲሆን ይህም የእናቶችና ህፃናት ህክምና በኮሮና ምክንያት ክፍተት እንዳይፈጠርበት የታሰበ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና እንዲሁም ስርዓተ ምግብ ዳይሬክተሯ ዶክተር መሰረት ዘላለም እንደ ሀገር የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል በተጨማሪ ለሌሎች ዘርፎች ትኩረት መሰጠቱን ገልፀው ከእነዚህ መካከል የእናቶችና ህፃናት ህክምና ቀዳሚው መሆኑን ገልፀዋል።
ለአዋላጅ ነርሶች የተደረገው ድጋፍም ይህንን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በአፈወርቅ እያዩ