ኮሚሽኑ በአዲስ አበባና በጋምቤላ በአጀንዳ ልየታ መድረኮች የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በጋምቤላ ክልል በሚካሄዱ የአጀንዳ ልየታ መድረኮች የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)÷ በአዲስ አበባ ተሳታፊዎችን የመለየቱን ስራ ለማከናወን እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላትን በመለየት ስልጠና መሰጠቱንና ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
በስልጠናው ከመምሀራን፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከእድሮች እንዲሁም ከወረዳ አስተዳደር የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።
ሰልጣኞች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በድምሩ 10 ሺህ የሚሆኑ ተሳታፊዎችን በመለየት ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ተወካዮችን የመምረጡ ሂደት አዲስ አበባ ላይ በሁለት ዙር የሚከናወን ሲሆን÷ ነገ በሚከናወነው የመጀመሪያው ዙር 60 ወረዳዎች ተካፋይ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በቀጣዩ ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ በተመሳሳይ ቀሪዎቹ 59 ወረዳዎች የሚሳተፉባቸው መድረኮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
በጋምቤላ ክልልም በ14 ወረዳዎች የተሳታፊ ልየታው የተጠናቀቀ ሲሆን÷ ተሳታፊዎቹ በክልሉ በሚካሄደው አጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ ነው ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በጋምቤላ ክልል ለሚካሄዱ የተወካዮች ውክልና ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።