በጋምቤላ ክልል በወንዞች ሙላት በ9 ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተፈናቀሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ወንዞች በመሙላታቸው ምክንያት ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የጋምቤላ ክልል መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡሞድ ኡሞድ እንዳሉት የአብዛኛው ሕዝብ አሰፋፈር ወንዞችን የተከተለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ÷ ባሮ፣ አልዌሮ፣ ጊሎና የአኮቦ ወንዞች ሞልተው ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡
በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በኑዌር ዞን የሚገኙ አምስቱም ወረዳዎች፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግና ጆር ወረዳዎች ላይ የውሃ መጥለቅለቅ ተከስቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የገለጹት አቶ ኡሞድ÷ ተፈናቃዮቹን ለጊዜው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እንዲጠለሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለማድረግ የአደጋውን መጠን የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም የወንዞቹ ሙላት ሊጨምር ስለሚችል ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!