ሙስናን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎች ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሙስና ና ብልሹ አሰራርን መከላከል እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ቀዳሚ አጀንዳዎች እንደሆኑ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለፁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የህዝብና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር ላይ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመዋል።
ማሻሻያው በፐብሊክ ሰርቪስ መዋቅር ብቻ ሳይገደብ በአመራር መዋቅር ላይም በመተግበር ያለ አግባብ ይባክን የነበረውን ሰፊ ሃብት ማዳን እንደተቻለ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የህዝብን ቅሬታ መነሻ በማድረግ በክልሉ ካሉ 85 ሺህ ያህል የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ውስጥ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የተባሉትን በመለየት የመፈተሽ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የ25 ሺህ ሰራተኞችን የትምህርት ማስረጃ ማጣራት የተቻለ ሲሆን÷ ከነዚህም ውስጥ ከ1 ሺህ 900 በላይ የሚሆኑት ማስረጃዎች ሀሰተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቁመዋል።
ሀሰተኛ ሆነው የተረጋገጡትን በህግ አግባብ አስፈላጊና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ መቻሉን ጠቁመው÷ በደመወዝና በሌሎች አግባብ ባልሆኑ ክፍያዎች ይባክን የነበረውን ከ84 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በ2015 በጀት ዓመት ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ የክልል፣ የዞን እና ወረዳ ተቋማት ላይ የኦዲት ፍተሻ በማድረግ በጥሬ ገንዘብ ብቻ ወደ 36 ሚሊየን ብር የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ማስመለስ እንደተቻለም ተናግረዋል።
በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ከህብረተሰቡ የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመታገል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በአፅንኦት ገልፀዋል።