አሜሪካ በሱዳን ግጭት ለተጎዱ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ከ130 ሚሊየን ዶላር በላይ ይፋ አደረገች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት ለተጎዱ የሚውል ከ130 ሚሊየን ዶላር በላይ ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ ይፋ አደረገች፡፡
ዋሺንግተን አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፉን የምትለቀው በአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) በኩል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ተወካይ ሳራ ቻርለስ በከፍተኛ ሚኒስትሮች ደረጃ በተዘጋጀው መርሐ-ግብር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ድጋፉ በሚሊየን ለሚቆጠሩ በሱዳን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ÷ የጤና ፣ የዓልሚ ምግብ ፣ የመጠለያ ፣ የንጹሕ ውሃ እና የንፅሕና መጠቀሚያዎችን ጨምሮ የተለያዩ አቅርቦቶችን ለማሟላት እንደሚውል ተገልጿል፡፡
መግለጫው ሰብዓዊ ዕርዳታ ብቻውን በሱዳን ለተከሰተው ግጭት እልባት ባይሆንም ሕይወት እንደሚታደግ አመላክቷል፡፡
ተፋላሚ ኃይሎቹ የሰብአዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመውረራቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ሁኔታውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም መግለጫው ጠቁሟል።
በመሆኑም ተፋላሚ ኃይሎች ጦርነቱን በአስቸኳይ እና በዘላቂነት እንዲያቆሙ እና ሰብዓዊ ድጋፉን እንዳያስተጓጉሉ ብሎም ለሰብአዊ ዕርዳታ ሰራተኞች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት የድጋፉን ተደራሽነትን ማረጋገጥ አለባቸውም ብሏል መግለጫው።
አሜሪካ ያደረገችውን የአሁኑን ድጋፍ ጨምሮ ለሱዳን እና የሱዳንን ተፈናቃዮች ተቀብለው ለሚረዱ ሀገራት እስካሁን 840 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ወጪ አውጥታለች፡፡
አሜሪካ ያደረገችው ድጋፍ ይፋ የሆነው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በተካሄደው የሱዳን እና የቀጣናው ሀገራት ሁኔታ ላይ በከፍተኛ የሚኒስትሮች ደረጃ በተሰናዳው መርሐ-ግብር ላይ ነው።